የዕድግ ታላቁ የትምህርትና የልማት ዕውቅና መርሐግብር በደመቀ ሁኔታ ተከናወነ
አዲስ አበባ አየር ጤና አንተነህ ሁለገብ አዳራሽ— ዕድግ-አቀፍ የትምህርትና ልማት ማስፋፊያ ድርጅት መስከረም 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ታላቅ የዕውቅና እና የሽልማት መርሐግብር ከ1,000 በላይ የማኅበረሰብ አባላት፣ ተማሪዎች፣ ተመራቂዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ አከበረ።
መርሐግብሩ በማኅበረሰቡ አባት በሃጂ ሺፋ ይማም ምርቃት የተከፈተ ሲሆን፣ በመቀጠልም መምህር መክብብ ገብረማርያም (የአዲስ አበባ የቅርስ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሞያ) እና ተካልኝ ሸዋለም በአማርኛ እና በጉራግኛ ቋንቋዎች ያዘጋጇቸውን ግጥሞች አቅርበዋል። መምህር መክብብ በዚሁ ወቅት በባህል፣ ኪነጥበብ እና ቅርስ ስልጠናዎችዙሪያ ለማኅበረሰቡ አባላት ነፃ የትምህርት እድል እንደሚያመቻቹ አብሥረዋል።
በዕለቱም ድርጅቱን በታማኝነትና በላቀ ደረጃ ላገለገሉ የቀድሞ የቦርድ አባላት የዕውቅና ምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የትምህርት ውጤት ሽልማቶችና ማበረታቻዎች
በመርሐግብሩ መስፈርቱን ያሟሉ በርካታ ተማሪዎችና ተመራቂዎች የተሸለሙ ሲሆን፡-
- የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች፡ ከ40 በላይ የ6ኛ ክፍል፣ 44 የ8ኛ ክፍል እና ከ62 በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተረክበዋል።
- የጥናት መጻሕፍትና የገንዘብ ሽልማት፡ ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የትምህርት መጻሕፍት የተሰጡ ሲሆን፣ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡት እንደየደረጃቸው 2,500፣ 3,000 እና 4,000 ብር ተበርክቶላቸዋል።
- የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች፡ ለሁሉም አልፊ ተማሪዎች በሒሳብ ቁጥራቸው 5,000 ብር የሚተላለፍ ሲሆን፣ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡት ስማርት ሰዓት ተሸልመዋል። በተጨማሪም ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ሰባት ተማሪዎች በበጎ ፈቃደኛ የማኅበረሰቡ አባል አማካኝነት ስማርት ሰዓት ተበርክቶላቸዋል።
- የላቀ ውጤት፡ 542 በማስመዝገብ የማኅበረሰቡ ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ሳሙኤል ታምራት ወለላ የ5,000 ብር ልዩ ሽልማት አግኝቷል።
- የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች፡ በዓመቱ ከተመረቁት መካከል 1 የዶክተር ዲግሪ፣ 2 በሕክምና እና በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኙ ተመራቂዎች ይገኙበታል። ለወንድ ተመራቂዎች ስማርት ሰዓት፣ ለሴት ተመራቂዎች ደግሞ የብር አንገት ሀብል ተሸልሟል።
የአጋሮች ዕውቅና እና የወደፊት አቅጣጫዎች
ድርጅቱ ለዚህ ስኬት አስተዋጽዖ ላደረጉ አጋሮቹ የፕላቲኒየም (50,000 ብር)፣ የወርቅ (30,000 ብር) እና የነሐስ (20,000 ብር) የዋንጫ አዋርድ እንዲሁም ባለ 10,000 ብር አጋሮች የመዳብ ደረጃ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
በመጨረሻም ድርጅቱ ለቀጣዩ ዓመት (2019 ዓ.ም.) የሚከተሉትን ዋና ዋና ማሳሰቢያዎች አስተላልፏል፡-
- የውጤት ማስገቢያ ጊዜ በጥብቅ የሚከበር በመሆኑ ከተቆረጠው ቀን ውጪ ተቀባይነት አይኖረውም።
- በ2019 ዓ.ም. ዕውቅና የሚሰጠው ለልዩ ተሸላሚዎች ብቻ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
- ለተመራቂዎች ሽልማት የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ማለፍ እንደ ዋና መስፈርት ይወሰዳል።
- ድርጅቱ ገቢውን ለማሳደግ ከባለሀብቶችና ባለሞያዎች ጋር የሚሠራበትን አዲስ የአጋርነትና የንግድ ማስተዋወቂያ አማራጮችን ያመቻቻል።
መርሐግብሩ በሦስት የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃትና በኬር ሥነ-ሥርዓት ፍጻሜ አግኝቷል።